ሰኞ 27 ኦክቶበር 2014

የሁለት እስረኞች አጭር ወግ

ባይኑ ቀለም ሰበብ
የታሰረ ጓዴን ልጎበኘው ሄጄ
"እስር ቤት እንዴት ነው?" ስለው ለወዳጄ
እንዲህ አለኝ ልጄ ...

" እስር ምንም አይል
ነፃነትን ገፎ ነፃነት ያለብሳል
ትንሽ አስረስቶ ትልቁን ያስመኛል።
ይልቅ ልጠይቅህ...
ትልቁ እስር ቤት በቃ ተመቻችሁ?
በ'ዛ ክፍት ጣሪያው
ፀሐይ እና ዶፉን ሲያዘንብባችሁ
ሲሳይ መሰላችሁ? "

ረቡዕ 22 ኦክቶበር 2014

ግር

ልክ እንደ በግ መንጋ
ግር ብለው መጥተው
መስኩን ግጠው ግጠው
አፈሩን ለንፋስ
አለቱን ለፀሐይ
አሳልፈው ሰጥተው
በመጡበት ብሂል
ግር ብለው ሊሄዱ
ድንገት ሲሰናዱ
ግር ይላል መንገዱ።

ማክሰኞ 21 ኦክቶበር 2014

ጥፋት

ትናንትናችንን - ካጋባስንበት የታሪክ ረብጣ
ዛሬያችንን - ከቸረቸርነው ለእለት ቂጣ
ነገአችንን - ከተበደርነው ባ'ራጣ
ለ'ኛ ካለ'ኛ - ማን አለን አጥፊ ባላንጣ።

ሐሙስ 16 ኦክቶበር 2014

ተስፋ

እንደ ወፍ ነው ተስፋ፣ ክንፎቹ አማላይ
በርሮ ፣ በርሮ ፣ 'ሚያርፍ፣
ከነፍስ ቅርንጫፍ ላይ።

ተስፋ ባለ ጥበብ ፣ ተስፋ ባለ ክራር
በረቂቅ ጣቶቹ፣
ነገን በዉብ ዜማ ፣ ቃኝቶ 'ሚደረድር።

ምን ነካው?

አፈሩ ምን ነካው?
አየሩ ምን ነካው?
ምን አገኘው ዉሃው?
በላመ ማሳ ላይ
ምርጥ ዘር ስንዘራ
ባ'ረም የተሞላ
እሾህ የሚያፈራ?