በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
በናፍቆት ሰቀቀን
በመገፋት ቆፈን
እንደማለዳ ዉርጭ አኮራምተኸኛል።
በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
ዱካህን አጥፍተህ በፈለግኩህ ጊዜ
ሰው አልባ አርገኸኝ ባገሬ በወንዜ
እንደቆላ ሃሩር አጠውልገኸኛል።
በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
ሆነክ ያልሆንከዉን
ኖሮክ የሌለህን
ስትቃዥ በቁምህ
ክፉ ህልሜ ሆነህ እንቅልፌን ነጥቀሃል።
በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
ዳብሰህ ሌላ ገላ
ጎርሰህ ሌላ ከንፈር
በቅናት ማዕበል አናውጠህ አዳፍተህ
ከሰው ተራ አውጥተህ
ከመሃል ዳር ገፍተህ
ከንፈሬን በጥርሴ አስነክሰኸኛል።
በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
እቶን ወላፈኑ በሚንቦገቦገው
በበደል ምጣድ ላይ አገላብጠኸኛል
አሻሮ እስኪወጣኝ እስካ'ር ቆልተኸኛል ።
በእርግጥ ጎድተኸኛል፣
ዉስጤ ግን ይልሃል......
ከበደል ከስቃይ ከበቀል ባሻገር
እጅ ባፍ እሚያስጭን የረቀቀ ሚስጥር
በልብ የሚዳሰስ ከስሜት ጥላ ስር
ማሪው ማሪው ይላል እውነተኛ ፍቅር።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ