About

ምን እግር ጣልዎት ጌታው? ወይስ እንደፈራሁት ጣቶትን ሰይጣን አሳስቶት ነው ክሊክ ያረጉት? መቸም ይሄ ሰይጣን የሚሉት ሰውዬ(?) ፈርዶበታል። የልቡን ያደረሰ ሁላ በሱ ያላክካል። ለማንኛዉም በመምጣትዎ ደስታዬ ሞልቶ ተርፏል። የእድለኛነትዎ ብዛት፣ አቦል ማኒፌስቶ ላይ ነው የደረሱት። አንድ ሲኒ ፉት ብለው ያዘግማሉ።

ስፈጠር ያለም ዜጋ ነኝ፣ በምርጫዬ ደግሞ ኢትዮጵያዊ። ኢትዮጵያዊነት ከዚያች ደጋግመን ከምንመዛት ኩራትና ክብር ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ልናነሳቸውም ሊነሱብንም ከማንፈልጋቸው ኮተቶቹ፣ ዉርደቶቹና ሽንቁሮቹ ጋር ፈቅጄ የለበስኩት ዜግነቴ ነው። ዶሮ ወጥ ወይ ክትፎ ስለበላሁ፣ ኢትዮጵያዊነትን አላገሳ። በባንዲራ ያሸበረቀ ሸማ የለበሱ ሰዎች ባጠገቤ ስላለፉ፣ ያገር ስሜቴ ከእንቅልፉ አይባንን። በባዕድ መንጋ መሃል አማርኛ ብሰማ ያገሬን ሰው አገኘሁ ብዬ አንገቴን አልቆለምም ጭራዬን አልቆላ። እስክስታ ባየሁ ቁጥር የሰማንያ ምናምን ብሄሮችን ዳንኪራ በትከሻዬ አልገፈትር።

የምኖረው እንደ ሰው ነው፣ በማሰብና በመጠየቅ። ከሚያወሩልኝ ይልቅ ሊነግሩኝ ያልፈለጉትን በንግግርዎ መሃል ስፈልግ ቢያስተዉሉ አይገረሙ። ከ "ምን ይሉኛል" ጋር ተላልፈናል፣ አይደርስብኝ አልደርስበት። ከርሶ በሃሳብ ተቧቅሼም ቢሆን ከራሴ ሽርክና ስምም ነኝ። ነፃነቴን አፍቃሪ፣ የሌላዉንም አክባሪ መሆኔ ለድርድር ባይቀርብም፣ ልክ እንደርሶ እኔም አልፎ አልፎ አምባገነንነት ያመኛል። በልብዎ "ይማርህ" ሲሉ ይሰማኛል። አሜን አብረን እንማር፣ ብቻዬን ተምሬ የት ልደርስ ምንስ ልከውን? ሳደምጥም ሆነ ሳነብ በዝግታና በጥርጣሬ ነው። ለሰባኪ የማልመች አይነት ነኝ። አንዳንዴ ተራ ጥያቄ ልጠይቅዎት እችላለሁ። ያኔ "እግዚኦ! እንዴት ያለው ደነዝ ነው" ብለው ጠበል ፍለጋ አይባዝኑ። ለርሶም ለኔም የሚበጀው ዲስኩርዎን አሻሽሎ ማቅረብ ላይ ቢተጉ ነው። ነገር ሲገባኝ በምርቃና ዘልዬ ጥምጥም ስልቦት ተረድቶ የማስረዳትን ጥግ ይረዱታል።

ይህ ገፅ ህላዌን በስነ-ግጥም መመርመሪያ እልፍኝ ነው። ላቅመ-መጋራት የደረሱ የመሰሉኝን ሃሳቦች በግጥም የምደረድርበት ሱቅ በደረቴ አይነት። ከምናውቀው ሱቅ በደረቴ የሚለየው፣ "ጀብሎ ጀብሎ" እያልኩ ያላፊ አግዳሚዉን ጆሮ አለማደንቆሬ። ልክ እንደርሶ ክሊክ ጥሎት የመጣ አንብቦ (ግፋ ቢል አሰላስሎ) ያልፋል። እስከዚህ ካነበቡ፣ በመንፈስ ተገናኘን ማለት አይደለ? መንፈሴን ዘረጋሁ፣ መንፈሶን ይዘርጉ። እንጨባበጣ! አይዞት ጠበቅ አርገው ይጨብጡኝ። መንፈስ እኮ ዘር የለዉም፣ ብሄርም፣ ፆታም፣ ቀለምም።

ምንም አስተያየቶች የሉም: