ሰኞ 15 ሴፕቴምበር 2014

ስለ ሞገደኛው ፍቅርሽ

ላወጋሽ ስከጅል ፣ ታሪኬን ዘርዝሬ
በትዝታ ክንፌ ፣ የኋሊት በርሬ
ድው! ድው! እያለ ፣ እንደ ጠንቋይ ዲቤ
በጉግስ ትርታ ፣ እየመታ ልቤ
ከወዳደቀበት ፣ ትንፋሼን ሰብስቤ
የድፍረትን አየር ፣ በረ....ዥሙ ስቤ
በብርክ ማዕበል ዉስጥ እንደተሳከረ
ከወዲያ ከማዶ ይጣራ የነበረ
አስገምጋሚው ድምፄ ፣ ጭጭ ብሎ ቀረ።

ሻል ያለኝ ሲመስለኝ
እንዲህም አስመኘኝ

ቃላት ከፊደላት ሰብስቤ
ሃሳብ ባ'ሳብ ላይ ደርቤ
አንደበቴ ተሞርዶ እንዳለቀ
ሃሳቤ ባ'ንዳፍታ ተፍረከረከ
ድንጋይ አንደመታው መስታወት ተሰነጠቀ።

በማዕበላማው የፍቅር ባህርሽ
ጀልባዬ ብትሰጥም አይግረምሽ
እንኳንስ የ'ኔ ኢምንት ጀልባ
ካንቺ ዉብ አይን ከቶ 'ማትገባ
ተወርዋሪው የፍቅርሽ ማዕበል
ግዙፉን መርከብም ያሰጥማል።

የፍቅርሽ ወጀብ ብርታቱ
ተተርኮ ላይዘለቅ ጥልቀቱ
ኮስማና ጀልባዬን አንስቶ
ካ'ለት ከቋጥኙ አጋጭቶ
ያረጀ አካላቷን ፈታትቶ
መደገፊያ ዘንጌን ነስቶ
አንደ'ዜ በፍቅርሽ ማዕበል ስደገፍ
ሌላ'ዜ በወጀቡ ተገፍቼ ስንሳፈፍ
ለይቼ ሳላውቅ ኩነቴን
መኖሬን ወይ አለመኖሬን
መሆኔን ቆሜ ሳበስር
አለመሆኔ ሲነቅለኝ ከሥር
በመኖሬ መኖር ሳጓራ
አለመኖሬ ገዝፎ ከጋራ
ወዲህ ረከስኩ ብዬ ስቆዝም
ወዲያ ዋጋዬ ንሮ ስደመም
ስሞት ስነሳ በፍቅር
ስለ ትንሣኤ መኖር
ከቶ እንዴት ብዬ ልጠራጠር?

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ