ሰኞ 26 ጃንዋሪ 2015

ከሁለት አጣሁ

እኔ ችግኝ ሆኘ ፣ አንች አትክልተኛ
መኮትኮቻሽ ዱልዱም ፣ ማረሚያሽ መናኛ
ለይቶልኝ አልጠወለግሁ
አድሎኝም አልለመለምሁ
ዳግም ላልጠረቃ ቀነጨርሁ።

ማክሰኞ 13 ጃንዋሪ 2015

እሪ በከንቱ

ከመሃል ፒያሳ ፣ ወደ እሪ-በከንቱ ፣ በወስደን መንገድ
እንደዋዛ አየናት ፣ ጠሐይ ያላመሏ ፣ በእሳት ስትማገድ
ምን ይልክ አፅሟ ፣ ምን ይልክ አጥንቷ
የ'ቴጌ ጣይቱ ፣ የልበ-ብርሃኒቷ
የትውልዴ ዜማ ፣ ድርድሩና ምቱ
እሪ ነው ፣ እሪ ነው ፣ እሪ ነው በከንቱ!    

ዓርብ 9 ጃንዋሪ 2015

ለምን ተሰደደ?

"ለምን ተሰደደ?" ፣ ለሚል ልብ አውላቂ
ጆሮዉ ለቆመበት ፣ መልስ-አወቅ ጠያቂ
ብላችሁ ንገሩት!

ለእልፍ አልፎ-ሂያጆች ፣ ጥላና ከለላ በነበረች ሀገር
በብዙሃኑ ላብ ጥቂቶች ሲኖሩ ታከተው ማኗኗር።
በመወለድ ቋንቋ ፣ በዜግነት ልኬት ፣ ምን ቢሆን አንደኛ
ቀና ባለ ቁጥር አንገት እያስደፉት ፣ በተዋረድ ወርዶ ፣ ቢሆን ሰባተኛ።
የመገፋት ጋራ ፣ መግፋት አንገሽግሾት
የበይ ተመልካች ፣ መሆን አቅለሽልሾት
ብላችሁ ንገሩት!

የሞተላት ሳይሆን ፣ ገዳይዋ ሊበላ
ሃገሩን በቅርጫ መበለት-መካፈል ፣ ባይሆንለት መላ።
ከችጋር ችንካሩ ፣ ተላቆ ሊራመድ
ስንዝር መሬት ቢያጣ ፣ በሮቹን ለመጥመድ።
የተከሰከሰው ያባቶቹ አጥንት ፣ አጥንቱን ቆርቁሮት
በትንባሆ ዋጋ ቀዬው ሲቸረቸር ፣ ቆሽቱን አሳርሮት።
ብላችሁ ንገሩት!

** ** ** ** ** **
"ለምን ተሰደደ?" ፣ ለሚል ልብ አውላቂ
ጆሮዉ ለቆመበት ፣ መልስ-አወቅ ጠያቂ
አሁንም ንገሩት!

በኡኡታው ፣ ቢመነጠር
በዝምታው ፣ ቢጠረጠር
ከመሃል ዳር ቢወረወር።
ብላችሁ ንገሩት!

በአብሮነት ጥማት ፣ በሃሩር ቢንቃቃ
በአድምጡኝ ተማፅኖ ፣ ጎሮሮው ቢነቃ
በልዩነት ደወል ፣ ከንቅልፉ ቢነቃ።

የነፃነት አሊፍ፣
የ'ኩልነት ሆሄ፣
የፍትህ ፣ የርትእ ፣ የፍርድ አቡጊዳ
ያልገባው ነፃ'ውጪ ፣ አንድ-ሁለት አስብሎ ቢያስቆጥረው ፍዳ
ብላችሁ ንገሩት!

** ** ** ** ** **

"ጨርቁን ማቁን ሳይል ካገር የበነነ
ምነው ወንድም-ዓለም እንዲህ የጨከነ?"
ብሎ ለሚጠይቅ መልስ-አወቅ ጠያቂ
ብላችሁ ንገሩት!  

ስጋዋ ተግጦ ፣ ደሟ ተመጥምጦ
አጥንቷ ተሰብሮ ፣ መቅኔዋ ተመጦ  
የሀገሩን ቅሪት  ፣ ቢያይ ልቡ ደምቶ
እሷን ሚያወሳው ፣ ምናምኒት ጠልቶ
ነፍሴ አውጭኝ ብሏል ፣ ከቀን ጅቦች ሸሽቶ።
ብላችሁ ንገሩት!
"ለምን ተሰደደ?" ፣ ለሚል ልብ አውላቂ
ጆሮዉ ለቆመበት ፣ መልስ-አወቅ ጠያቂ።