ቅዳሜ 5 ሴፕቴምበር 2015

በዘመን ባቡር ላይ

ለሰርክ ነጓጁ ፣ ብርቁ ላይደል ጉዞ
ክፉኛ ይከንፋል ፣ ባለጊዜ ብቻ በሆድ'ቃው ይዞ
ወደ አዲስ ዘመን ፣ተጓዥ እየጠራ
ሂያጁን ከሚቀረው ፣ ለቅሞ እያጠራ
የጊዜ ባቡሩ ፣ያልፋል እያጓራ።

ከውራ ፉርጎ ላይ ፣ እኔ አለሁ እንዳለሁ
ለጉድ የጎለተኝ ፣ ጭሱን እምጋለሁ
ጭሱን ገምሶ አልፎ ፣ ነፋስ ያወጋኛል
የዘመን ቱሩፋት ፣ ተስፋ ያበስረኛል
መጪው እኮ አደይ ነው ፣ እያለ ያፅናናኛል
ጨለማና ጭጋግ ፣ ሂያጅ ናቸው ይለኛል።

እኔ ደግሞ እላለሁ፣
"እብሪተኛን ሁላ ፣ በክንዴ እንዳልመከትሁ
ከአለትም አለት ፣ ሮሃን እንዳልነበርሁ
እንደ እፉዬ ጋላ ፣ ቀለለኝ ገላዬ
እንደሰማይ ኮከብ ፣ 'ራቀኝ ጥላዬ
እንደ ሙታን መንደር ፣ ጭራ'ለ ጓዳዬ
ከዘመን ገደል ዉስጥ ፣ወድቆ ገመናዬ።"

ቀጠለ ነፋሱ ጭስ እየገመሰ
ባቡሩም ገስግሶ ካንድ ዋሻ ደረሰ
ፍልፍል ያለት ዋሻ
ጣራው የነተበ በጭስ በጥቀርሻ
ከሩቅ ይጠራኛል ባማላይ ጥቅሻ

እንዲህ 'ሚል መስሎኛል፣

"ባታውቀው ነው እንጂ፣ ባታሰላስለው
ይህ ዋሻ አንተ ነህ፣ ጥቀርሻው ላብህ ነው
በዘመን ድማሚት ፣ በባለቀን መሮ
ወዘናና መቅኔህ ፣ ጅስሚህ ተቦርቡሮ
ይህ ዋሻ ታንፀ ፣ ካንተ ደምና'ጥንት
ባለጊዜ ብቻ ፣በፈጣኑ ባቡር ፣ እብስ እንዲልበት።
ካሮጌ ፍስሃው ፣ ወዳዲሱ ተድላው ፣ እንዲሻገርበት።"