ሰኞ 17 ጁላይ 2017

አእምሮ ከሰማይ ይሰፋል

አእምሮ ከሰማይ ይሰፋል፣
መሳ ለመሳ ቢቀመጡ
አንዱ ሌላዉን ሳያቅማማ መሰልቀጡ።
አእምሮ ከባህር ይጠልቃል፣
መልክ ለመልክ ቢነፃፀሩ
ባልዲ ዉሃ በስፖንጅ እንዲመጠጥ
እንዱ በሌላው ባፍታ ይጨለጥ።
ያ'እምሮ ሚዛን ልኬቱ
አቻ ነው ከፈጣሪው ከጠበብቱ
እፍኝ ለእፍኝ መዝኖ
ኪሎ ለኪሎ ተምኖ
አንዱን ከሌላው መነጠል
ድምፀትን ከድምፅ እንደመፍተል።
--------------
መነሻ: "The Brain -is wider than the Sky" -- Emily Dickinson

ዓርብ 7 ጁላይ 2017

ነገን

ቅንጣት ሳይጠብብን፣ የጥበት ስፋቱ
ከቶ ሳይጋርደን፣ የፅልመት ፍካቱ
ወትሮ ሳያንስብን፣ የማነስ ግዝፈቱ
ሞልቶ ሳይፈስብን፣ የባዶ ሙላቱ
ከሃሴት ከረጢት፣ ስሜት ተሰድሮ
ከምናብ ጋን ሙላት፣ ክዳን ተስፈንጥሮ
የሀቅን ወለላ፣ ጨለጥናት ባንዳፍታ
የኋሊት እያየን፣ ነገን በትዝታ።