ደማቅ ከዋክብት ፣ ከልባቸው እየሳቁ
እኔና እንቺን ብቻ ፣ በደስታ ሲያጠምቁ
ጨረቃዋም ፣ ፈክታ በተራዋ
ስታስጌጠን ፣ በጣፋጭ ፈገግታዋ
በፍቅርሽ ምትሃት ፣ ተዘውሬ
ብቅ እላለሁ ፣ እንደገና ተፈጥሬ።
አንድም ቃል ፣ ካንደበታችን ስይወጣ
ጮክ ብለን ስናወጋ ፣ ፍፁም በፀጥታ
ፈውሰ-ፍቅርሽ ፣ በደሜ ናኝቶ
ህመም መከራዬን አሰናብቶ
የጊዜ ዑደት፣ ሕጉ ላልቶ
ያሳለፍናቸው ፣ እልፍ ቀናት
ያጥሩብኛል ፣ እንደ ቅፅበት
አይን ጨፍኖ ፣ እንደመክፈት።
አዋቂ አስተዋዮች፣
መተንፈስ ሲከለከሉ
ወይ ስጠፈነጉ ፣
ወይ ሲገፉ እስኪወድቁ
ያላዋቂ ታዋቂዎች፣
በሚያነሱት የሐሰት አቧራ
የማስተዋል ጉንፋን ያዘን፣
ማስነጠሱ የማያባራ
ያላዋቂነታቸው ግዝፈቱ፣
እንደ ህዋ ስፋቱ
እንደ ዉቅያኖስ ጥልቀቱ
ሲገላበጥ መዝገበ-ቃላታቸው፣
ሆድ እንጂ ህሊና አያስነብባቸው
የመጣዉን መስሎ አዳሪ ፣
ለማሽቃበጥ ፊታውራሪ ፣
ሆድ ለመሙላት ብቻ ኗሪ
ለተንሸዋረረው አይነ-ህሊናቸው፣
የትዉስት ነው መነፅራቸው ፣
አሱም አርቆ አያሳያቸው
አለማወቃቸዉን ባለማወቃቸው
ትዉልድ ይሻገራል ድንቁርናቸው።