ከቶ አትጠየቅ "ለምን?" ትብለህ
ምን አሳቀቀህ ፣ ማን ሊሞግትህ
እንዳሻህ ጠርቅ ፣ ተርትር ነገርህን
የ "አሉ" ቱባ ፣ የወሬ ክምርህን
ሎጋ ምላስህን ፣ ሳለውና
በሾለው በኩል ፣ ሞርደውና
ቁረጥ ፣ ዘልዝል ፣ የወሬ ሻኛ
"ታመመ" ሲሉህ ፣ "ሞተ" በል ለእኛ
እኛ እንደሆንን፣
"ለምን?" ፣ "እንዴት?" 'ማይገደን
በ "መሰለኝ" ባህር የተወዘትን
የምይሞቀን ፣ የማይበርደን
ለምላስ ጀግና እጅ የሰጠን
ኩሩ የ "አሉ" ምርኮኞች ነን።