ሰኞ 16 ማርች 2015

ሾሙልኝ

እንደማነባ ቀድመው አውቀው
ለልቅሶዬ ደህንነት ተጨንቀው
ሾሙልኝ እንባ ጠባቂ
ላያስጥለኝ ከነጣቂ።

አቤቱ

የፍርሃቴ ዝንበት ፍጥነቱ
ከካፊያ ወደ ዶፍ ምጥቀቱ
የድፍረቴ ጤዛነቱ
በጫጉላ ጠሐይ ትነቱ
የልቤ ድምታው ድቤነቱ
ከቤተ-ደረት ማስተጋባቱ
ለግርማ ሞገስሽ ለሴትነቱ።

እሑድ 1 ማርች 2015

የዜግነት ነገር

እኔስ ብዬ ነበር፣
ዓለም ናት ሃገሬ
የሰው ዘር ነው ዘሬ
ወንዛ ወንዙ ወንዜ ፣ ሰፈሩ ሰፈሬ።
እኔስ ብዬ ነበር፣
ስፍሩ ነው ስፍሬ
ቁጥሩ ነው ቁጥሬ።
እኔስ ብዬ ነበር፣
አርቆ ላጤነው ፣ ከቅዥት ባሻገር
ሕልሜ ድንበር-የለሽ ፣ አድማስ'ሚሻገር።
እኔስ ብዬ ነበር ፣ ሰው ሁሉ ያገሬ ልጅ
ማጀቱ ማጀቴ ፣ ደጃፉ ለኔም ደጅ።
ካለም ተነጥዬ ፣ ካገር እንድረጋ
ሳልወድ ለጠፉብኝ ፣ ፓስፖርት ይሉት ታርጋ
ብጎመዥ ብቋምጥ ፣ ላልሆን ያለም ዜጋ።