እሑድ 1 ማርች 2015

የዜግነት ነገር

እኔስ ብዬ ነበር፣
ዓለም ናት ሃገሬ
የሰው ዘር ነው ዘሬ
ወንዛ ወንዙ ወንዜ ፣ ሰፈሩ ሰፈሬ።
እኔስ ብዬ ነበር፣
ስፍሩ ነው ስፍሬ
ቁጥሩ ነው ቁጥሬ።
እኔስ ብዬ ነበር፣
አርቆ ላጤነው ፣ ከቅዥት ባሻገር
ሕልሜ ድንበር-የለሽ ፣ አድማስ'ሚሻገር።
እኔስ ብዬ ነበር ፣ ሰው ሁሉ ያገሬ ልጅ
ማጀቱ ማጀቴ ፣ ደጃፉ ለኔም ደጅ።
ካለም ተነጥዬ ፣ ካገር እንድረጋ
ሳልወድ ለጠፉብኝ ፣ ፓስፖርት ይሉት ታርጋ
ብጎመዥ ብቋምጥ ፣ ላልሆን ያለም ዜጋ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ