ዓርብ 19 ጁን 2015

ላንድ የዋህ ፈረንጅ

<<እየደጋገመ ጠኔ ሚጥላቸው
ያንተ ሀገር ሰዎች ረሃብተኞች ናቸው>>
ላልከኝ የዋህ ፈረንጅ
መልስ አለኝ የሚፋጅ...
ምንም ባዶ ቢሆን ፣ አንጀት ማጀታቸው
የኔ ሀገር ሰዎች ፣ ርቅቅ ያሉ ናቸው
ጦማቸዉን አያድሩም ፣ ጦማቸውን አንደዋሉ
ጎናቸው አርፎ አያውቅም ፣ አንድ ነገር ካልበሉ።

ሐሙስ 18 ጁን 2015

ዞትር ሕያውነት

በትቢያነቱ ጊዜ፣
ከፍግ ተዳብሎ ተጣለ
ለምለም ሣር ሆኖ ከች አለ!
በሣርነቱ ዘመን፣
በጥርስ መንጋ ተጋጠ
ተመዥጎ ተሰለቀጠ
ከድቀቱ ዉርጅብኝ ፣ በሬ ሆኖ አመለጠ!
በበሬነቱ ጊዜ፣
አፈር ሲገፋ ሰነበተ
ባንዲት የቁርጥ ቀን። ታርዶ ተበለተ
አፅሙን በሥጋ ሸፍኖ ፣ ሰው ሆኖ ተከሰተ!
እሱ እቴ፣
ሰርክ ኗሪነቱ እየደረጀ
ላዲስ ህይወቱ ጥርጊያ መንገድ እያበጀ
ዞትር ይመጣል ሄደ ሲሉት
በገደብ አልባ ሕያውነት።

እሑድ 14 ጁን 2015

ጊዜና ትዝታ

መንገዴን ልቃኘው፣ ሳማትር ወደፊት
ሽምጥ ይጋልባል፣ ጊዜ ከፊቴ ፊት
አንገቴን ባዞረው፣ ለኋሊት ምልከታ 
ይዞኝ እብስ ይላል፣ እጅሬ ትዝታ።
ምንም ቢጠፍረው ፍርደ-ገምድል ዳኛ
ነገ ይፈታዋል የዛሬን እስረኛ።
በር አደርገዋለሁ፣ በሚል ከንቱ ተስፋ
መቅኔህን አትጨርስ፣ ግድግዳ ስትገፋ።

ሀ...ሐ

"ሀ..." ቢል በሀሌታው
"ሐ..." ቢል በሐመሩ
ፍቺው ላይለወጥ ፣ የክፍት አፍ ግብሩ።
ከ "ልክነት" እና ከ "መሳሳት" ወዲያ  
ካለው የነፍስ አምባ ፣ እንገናኝ ከዚያ።

ወጥ ረገጥክ

ችግሬ ያልገባው "ወጥ ረገጥክ" ይለኛል 
እንኳንስ እረግጠው እጎርሰው ጨንቆኛል