ጥሬ እኔን ሲያሞክኩ ፣ ከስለው በዚያው የቀሩ
ብሌናቸዉን ያሟሙ ፣ የኔን አይኖች ሲያበሩ
ቃራሚ ጆሮዬን ሲስሉ ፣ መስሚያቸው የዶለዶመ
ድዌዬን ዞትር ሲያክሙ ፣ ኩለንተናቸው የታመመ
እነማን እንደነበሩ፣
እስቲ ይታወሱ እነርሱ
እስቲ ይታወሱ በስሱ።
በደማቸው እንድወፍር ፣ ሞጌያቸው ፈጦ የወጣ
ወዛቸው አመዴን ሲያብስ ፣ ገጥታቸው የገረጣ
የደም ገንቦየን ሲሞሉ፣ የደም ሥራቸው የነቃ
ዋስ ምስክር ላጥቱ ፣ ለኔ እንዳልቆሙ ጠበቃ
እነማን እንደነበሩ፣
እስቲ ይታወሱ እነርሱ
እስቲ ይታወሱ በስሱ።
ባለጌ አንገቴን ሲያቀኑ ፣ ጭምት አንገታቸው የተደፋ
ሳንቃ ደረታቸውን የሰጡ ፣ ሸምበቆ ደረቴን እንድነፋ
የፍዳ ባህር ሳቋርጥ ፣ ሰርጓጅ መርከቤ የነበሩ
የመከራን ወንዝ ስሻገር ፣ ተጋድመው ድልድዬን የሠሩ
ደስታና ኡምራቸውን ፣ በአንድነት ለኔ የገበሩ
እነማን እንደነበሩ
እስቲ ይታወሱ እነርሱ
እስቲ ይታወሱ በስሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ