ቅዳሜ 2 ሴፕቴምበር 2017

እሳትና ዉሃ

እብሪት እንደዝናር፣ አጥብቀው በሚያስሩ
ክብሪት እንደክራር፣ በሚደረድሩ
በእፍባዮች ምድር፣ በቆስቋሾች ዓለም
መሆንህን ረስተህ፣ አንድ ዘለላ ፍም
የኔን ጠብታነት፣ ቁልቁል እያየሃት
መሆንህን ነገርከኝ፣ የማትከስም እሳት

እድሜ ለዝናቡ፣
አጭዶ ለሚወቃው፣ የዶፉን አዝመራ
ተግቶ ለሚሞላው፣ የውቅያኖስ ጎተራ
ምስጋና ለንፋስ፣
ሳይታክት ለሚሰጥ፣
ለጡዘትህ ቤንዚን
ለእብደትህ እስትንፋስ
 
ባንድነት ለመጥፋት፣ እንዳልተፋለግን
እልፎች እንዲፀድቁ፣ አብረን ጠወለግን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ