ዓርብ 29 ኖቬምበር 2013

ሀገሬ ወዴት ናት?

የሚያወጉባት ፣ ዜጎች በነፃነት፣
የሚነገርባት ፣ ከሐሰት ይልቅ እውነት፣
እኩል 'ሚታይባት ፣ ሁሉም ከሕግ ፊት፣
የሚከበርባት ፣ የዲሞክራሲ መብት፣
መንግስት በሃይማኖት ፣ እጅ የማይሰድባት፣
የዘራዉን ብቻ ፣ ሁሉም የሚያጭድባት፣
ሲኖሩባት እንጂ ፣ ኖሬ ያላየኋት፣
በናፍቆት ሰቀቀን ፣ አቅሌን ሳልስትባት፣
ሀገሬ ኢትዮጵያ ፣ ዉሰዱኝ ወዴት ናት?

ሐሙስ 28 ኖቬምበር 2013

መስታወት ጓደኛ

በሸንጋይ ፈገግታ ፣
በሳቅ ጭስ የሚያጥነኝ
ሲቸግረው ብቻ ፣
ፈልጎ እሚያገኘኝ
እኔ ስፈልገው ፣
ደብዛው የሚርቀኝ
አንድም ቀን ድክመቴን ፣
ደፍሮ ያልነገረኝ
እንዲህ አይነትማ ፣
እልፍ ጓደኛ አለኝ
እኔን የናፈቀኝ ፣
አጅጉን የራበኝ
እንደመስታወቴ ፣
ብጉር ጠባሳዬን በግልፅ የሚያሳየኝ።

ረቡዕ 27 ኖቬምበር 2013

የማስመሰል ኑሮ

መምሰል ከፊትለፊት ፣ መሆን ወደጓሮ
የምናወራዉን ፣ ኖረን ቢሆን ኖሮ
ባልቀረ ነበረ ፣ ሀገር ተንሸዋሮ ::

አስመሳይ አፍቃሪ

ወድሻለሁ ማለት፣
                    አርባ ክንድ የራቀው
ዉዱን በማራከስ፣
                   ቤት ዉስጥ የታወቀው
አይን ሲያርፍባት፣
                    በአይን ከምታውቀው
መውደዱን ይለብሳል፣
                      ቤት ደርሶ አስኪያወልቀዉ::

አስመሳይ ሰባኪ

መንፈሳዊ  ምግብ ፣ ቀን ሲመግብ ዉሎ
ደግ ደጉን እንጂ ፣ ክፉን ራቁ ብሎ
ማታ ያገኙታል ፣ ካባዉን አቅልሎ ::

አስመሳይ ዲሞክራት

'እኔን ካልሰማችሁ' ፣
'ሰማይና ምድር ተከደነባችሁ'
እያለ እሚያሳቅቅ ፣
አዉራ አምባገነን መሆኑን አውቃችሁ
አደባባይ ወጥቶ ፣
'ካለኔ ዲሞክራት ላሳር ነው' ሲላችሁ
ለይምሰል አድናቆት ፣
እጅ ከነሳችሁ
ታዲያ አናንተ ከእርሱ ፣
በምን ተሻላችሁ?

ማክሰኞ 26 ኖቬምበር 2013

ከተሸከማችሁን!

ነፃ አወጣናችሁ ፣ ካምባገነን ላንቃ
የድል ችቦ አብሩ ፣ ጭቆና አበቃ
ከዛሬ ጀምሮ ፣ ሕዝብ ነው አለቃ

በሕላችሁን ኑሩ ፣ ዳንኪራም ጨፍሩ
በማንነታችሁ ጭራሽ አንዳታፍሩ
ስም ስትጠየቁ ፣ ዘራችሁን ቁጠሩ

በጎጥ ወንዝ ገድበን ፣ የሸነሸናችሁ
በኛ ረቂቅ ጥበብ ፣ ከቶ እንዳይመስላችሁ

በዉሸት ስንሰብክ ፣ አሜን አያላችሁ
በቀደድነው ቦይ ዉስጥ ፣ እየፈሰሳችሁ
ጀርባችሁ ጠንካራ ፣ ወገባችሁ ምቹ
አኛን ለማስጋለብ ፣ ሰርክም አትሰለቹ

ፈቃዳችሁ ሆኖ ፣ ከተሸከማችሁን
መቁረጥ ተስኗችሁ ፣ ካደላደላችሁን
በልስልስ ጫንቃችሁ ፣ እንመቻቻለን
ታግሎ የሚያወርደን ፣ ካጣን ምን ጨነቀን!

ሰኞ 25 ኖቬምበር 2013

ድንቄም ልሂቅ

ፊደል መቁጠር  ከቶ ድንቁ
ማዕረግ ለሱ ቀለብ ስንቁ
የራስ ክብር እንቁ ወርቁ
አላውቅም ማለት ጭንቁ
መተባበር ለሱ ብርቁ

ባፉ ለወገን ተቆርሪ ፣
ዞር ብሎ ጉግድ ቆፋሪ
የወረቀት ላይ አንበሳ  ፣
በብዕር ተከልሎ የሚያገሳ

እራሱ በፍርሃት ርዶ
ምስኪን ወገኑን ማግዶ
በርግጎ ከሀገር ነጉዶ

በወገኑ ደምና አጥንት ፣
የለውጥ ጀምበር ይናፍቃል
እሱ ሰፊ አፉን ሊከፍት ፣
ሰፊዉን ህዝብ ይማግዳል።

የበይ ተመልካች

 ያ የጥንቱ አርበኛ ፣ ደሙን ያፈሰሰዉ
የሀገርን ድንበር ፣ አስከብሮ ያለፈው
ቀና ብሎ ቢያየን ፣ ምንኛ በቆጨው
የበይ ተመልካች ፣ ሆነን ሲታዘበዉ።