ሐሙስ 29 ሜይ 2014

ምፀት

በጠራራ ሌሊት ፣ በብሩህ ጨለማ
ይሞቀኛል ገላሽ ፣ አልደርብም ሸማ 
ይታየኛል ፊትሽ ፣ አልለኩስም ሻማ።

ብራና

ጥበብህ ተዳፍኖ ፣ እንዳትቀር መና፤
ፅልመቴ ተገፎ ፣ ዉልግዴ እንዲቃና፤
ከጋንህ ተላቀህ ፣ አሳየኝ ብራና።

እሑድ 25 ሜይ 2014

ትከሻ

አፈርማ አይደለም ፣ እምራመድበት፤
በድን መሬት አይደል ፣ በእግሬ የረገጥሁት፤
ባማተርሁኝ ቁጥር፣ በተንጠራራሁኝ፤
ከፍ አርጎ አያሳየ ፣ ነገዬን ያስቃኘኝ፤
ቁሞ የተሸከመኝ ፣ ወድቆም የደገፈኝ፤
የእልፎች ትከሻ ነው ፣ አፅንቶ ያቆመኝ።

ሐሙስ 22 ሜይ 2014

ተጓዥ

ቀኑን ፣ ስጓዝ፤
ዉዬ ፣ ስጋዝ፤
ምሽቱን ፣ ተቀብዬ፤
ካረንጓዴው ፣ ማሳዬ፤
በጀርባዬ ፣ ተንጋልዬ፤
አኝጋጥጬ ፣ ከሰማዬ፤
ባብረቅራቂ ክዋክብት ታጅበን፤
እኔ እና እኔ ፣ ጭልጥ ብለን ጠፍተን፤
አቅጣጫ አልባ ፣ ተጓዥ ሁነን፤

በፍጥነት እየከነፈ...............

ደራሽ ፍርሃት ፣ ልቤን ገምሶት አለፈ፤
የረሳሁት አገረሸ ፣ ያላየሁት አሰፈሰፈ፤
እረፍት አልባው እኔነቴ፣
ሰዉ-ነቱ ተንዘፈዘፈ።

እኔ ወደ እኔ ዘንበል ስል..........

የመጣሁበትን ፣ ሳብሰለስል፤
ያልሄድሁበትን ፣ ባይነ-ህሊናዬ ስስል፤
የማላውቅ ፣ ልዉጣ ልግባ፤
ሆንሁኝ ተጓዥ ፣ መሪ አልባ፤
መድረሻ ፍለጋ እምዳክር፤
በመንገድ አልባ ምድር።    

ማክሰኞ 20 ሜይ 2014

አመድና ዱቄት

በንፋስ ታንኳ ላይ ፣ አብረው ሽው እያሉ
አመድና ዱቄት ፣ በሳቅ ይፈርሳሉ።

ሰኞ 19 ሜይ 2014

ህልሜ

ራሷን በራሷ ነክሳ፣
           ደመ-ከልብ ከሚሆን ደሟ
አጥንቷን ባጥንቷ ሰብራ፣
           ከምትደፋ ባፍጢሟ
ባብራኳ ክፋይ ሟች-ገዳይ፣
           ዞትር ደረቷን ከምትደቃ
ማየት ነው ህልሜ ተስፋዬ ፣
          እናቴ ከእናቷ ታርቃ።      

ዓርብ 16 ሜይ 2014

የቸገረ ነገር

ያብሮነት ሲሆን መዝሙሩ፤
ክርሮ ከተወጠረ ደም-ሥሩ፤
የብርሃን ጎዳና ስትጠቁመው፤
የፅልመት ጉራንጉር ከዋጠው፤
አይኑ እያየ የሰው ምስል፤
ልቡ ክፉ አዉሬ ሲስል፤
ባንድነት አልጋ ተተኝቶ፣
በልዩነት ደወል ከተነቃ፤
ዛሬን ማለፍ ዳገት ሆኖ፣
ነገም ዘበት ሆነ በቃ።

ሐሙስ 8 ሜይ 2014

አንቺን ያገኘሁ 'ለት

አንቺን ያገኘሁ 'ለት፥

ቁሩን አንዳልሸኘች፣
               ምድሪቱን አሙቃ፤
ፀሐይ ያላመሏ፣
               ዋለች ተደብቃ፤
ካንቺ ትንፋሽ በላይ፣
               እንደማትሞቅ አውቃ።

አንቺን ያገኘሁ 'ለት፥

የሊቅ የደቂቁን፣
               ቀልብ አንዳልሰለበች፤
ሽሙንሙን ጨረቃ፣
               ደመና ለበሰች፤
ካንቺ ዉበት ልቃ፣
               ልቤ ስላልገባች።

አንቺን ያገኘሁ 'ለት፥

ዞትር በምሽቱ፣
               አይኔን 'ሚያዋልሉ፤
"ከኛ ወዲያ አድማቂ ተገኘች"፣
               እያሉ፤
ክዋክብት ለክብርሽ፣
               ከሰማይ ዘለሉ።

ማክሰኞ 6 ሜይ 2014

እስራት

አይደለም መቀፍደድ፣
               በብረት ሰንሰለት፤
አይደለም መከርቸም፣
               በዝግ ጨለማ ቤት፤
አይደለም መወርወር፣
               ከምድር በታች ግዞት፤
አይደለም መነጠል፣
               ከሰው መንጋ ምቾት፤
የመጠፈር ወጉ፣
የመሸበብ ልኩ፣
የመታሰር ጥጉ፤
በህሊና ወህኒ፣
              መንፈስ መጠፍነጉ።
በህሊና ችሎት፣
             ፍትህ መጠውለጉ።

ሰኞ 5 ሜይ 2014

መስለን

እንዳልከተልሽ፥
ጀርባሽ ፣ ጎራንጉሩ፤
እንዳላስከትልሽ፥
ጀርባዬ ፣ ሰንበሩ፤
የቁርጥ ቀን መጥቶ ፣ እስኪያፋጥጠን፤
እናዝግመው እንጂ ፣ ሁነን ጎን-ለ-ጎን፤
ለተከታያችን ፣ መስለን የተማመን።

ልትለኝ ፈልገህ...

በዚያች ዕለተ - ብሽቅ፥
በዚያች ጠዋተ - እንቅ፥
ባዲስ ተስፋ ጮራ፣
                   አይኖቼ የፈኩ፤
ያንተም ያለወትሯቸው፣
                   የተገረበቡ፤
በዝጉ አንደበትህ፣
                   ተረግዞ ነው መልእክት?
ለማዋለድ ነበር?፣
                   ያይኖችህ መዋተት
ምነው ባገር ሰላም?፣
                   ጠግበህ ማታገሳ
ትንፋሽ ራቀህ'ሳ፤
                  ተርበተበትህ'ሳ?
በቃህ ተንበረከክህ?
እጆችን ሰጠህ?
ጭራሽ ተመቻቸህ?
ክንድህ ትራስ ሆነህ?
*     *      *      * 
በዚያች ዕለተ - ብሽቅ፥
በዚያች ጠዋተ - እንቅ፥
ትዉስ ባለኝ ቁጥር፣
                  ያይኖችህ ዋተታ፤
                  የጆችህ ቧጠጣ፤
"በነበረው..." እላለሁ፣
ቅራፊ እስትንፋስ፣
                  ሽራፊ ደቂቃ፤
ምላስ ለማላቀቅ፣
                  ከደረቀ ላንቃ።


*     *      *      * 
ትዉስ ባለኝ ቁጥር፣
                  ሰርክ ይወጋጋኛል፤
                  ይሸነቁጠኛል፤
ልትለኝ ፈልገህ፣
                  ላትለኝ የቻልከው፤
አይንህ እንደዋተተ፣
እጅህ እንደቧጠጠ፣
ወዳይቀሬበት፣
                  ይዘህ የወረድከው።