በሰው መንጋ ተከብቤ
እውነት ሲሆን ጥሜ ራቤ
የሀቅ ልሳን ግቷ ነጥፎ
ክህደት ሲያዳፋኝ ጠልፎ
በቅጥፈት ጥላሸት ተለቅልቄ፣
በብቸኝነት ስለከሰልኩ
ዋሾ ወዳጄን ሸኝቼ፣
ታማኝ ባላንጣዬን ተቀበልኩ።
ሳያማትር ዙርያ ገባውን፤
ሳያደምጥ የገዛ ጆሮዉን፤
ባንክሮ አቀርቅሮ ከዘንጠለ፤
ሲጠሩት "አቤት" ካላለ፤
ድምፅ ፣ ትንፋሹን አምቆ፤
ጥላ ፣ ኮቴዉን ደብቆ፤
የበላኝ ጅብ ፀጥ ካለ፤
ከሁለት አንድ ነገር አለ...
ወዲህም ላይጠራ ቢጤዉን፤
ወዲያም ባይሞላ ስልቻውን።