ረቡዕ 22 ፌብሩዋሪ 2017

ተጓዥ

ከቶ ያልጠበበኝ፣ የጥበት ስፋቱ 
ቅንጣት ያልጋረደኝ፣ የፅልመት ፍካቱ 
ተጓዥ ነኝ መሪ አልባ
ያለየልኝ ልዉጣ ልግባ
መድረሻ ፍለጋ 'ምዳክር
በመንገድ አልባ ምድር።

ያቆዩት ሕልም

ምን ይሆን ዕጣፈንታው፣ ሕልምን በይደር ሲያቆዩት?
ፀሐይ እንዳሸው ቴምር፣ ይሟሽሻል ይደርቃል?
ወይስ እንደ መረቀዘ ቁስል፣ በመግል ጠበል ያጠምቃል?
እንደ ከረመ ሥጋ፣ ክርፋቱ ከሩቅ ይጣራል?
ወይስ እንደ ጣፋጭ ጭማቂ፣ የስኳር ኮረት ያበቅላል? 
 ምናልባት፣አንደ ከባድ ሸክም፣ ከላይ ወደታች ይጫናል? 
ወይስ ቀን ሞልቶ ሲፈስ፣ ተወጥሮ ይፈነዳል?
------
መነሻ: "Harlem", Langston Hughes

ጀግና

ለወገኑ ሟችም
ወገኑን ገዳይም
ባንድ ቁና ስፍር፣ ይባላሉ ጀግና 
ለሰው 'ሚታየው፣ እንደየቆመበት ይለያያልና።

ምኑን

ኡኡታ ካስመነጠረ 
ዝምታ ካስጠረጠረ
ዋቲው በተድላ ካልዋለ
ማቲው በረካ ካላደረ
የመጠላለፍ ፈንጣጣ 
ባ'ጋርነት ጠበል ልፍልፎ ካልወጣ 
የ'ንባ ተራራ ካልተናደ 
 የበደል መጋረጃ ካልተቀደደ 
መዥገሮች ከትከሻ ካልወረዱ 
ዳኞች በሀቅ ካልፈረዱ 
 ገበታው ካልቀረበ ያለስጋት 
ወጉ ካልተወጋ ያለፍርሃት
ምኑን አዲስ ቀን መጣ 
ምኑን አደይ ፈነዳ 
ምኑን አየን አበባ 
ምኑን መስከረም ጠባ!

ነገ

ከሃሴት ከረጢት 
ስሜት ተሰድሮ 
 ከምናብ ጋን ሙላት 
 ክዳን ተስፈንጥሮ
የሀቅን ወለላ ጨለጥናት ባንዳፍታ 
የኋሊት እያየን ነገን በትዝታ።

ጉዞ

ዝግ በል ከ'ርምጃህ 
ቆም በል ከጉዞህ 
ጠይቅ መድረሻህን 
ሞግት መነሻህን
መንጋው ሲያለከልክ፣ማጣፊያው ሲያጥር 
 ትርታህን አድምጥ፣ እምነትህን አንጥር።