ሐሙስ 20 ኤፕሪል 2017

ተፈጥረሃልና

በእኔና አንተ ምድር፣
ሆነህ አትፈጠር፣ ችግኝ ባለ ተስፋ
ከቶ ብቅ አትበል፣ በኮትኳች ልትፋፋ።
ባርባ ቀን እድልህ፣ ብታመልጥ ከ'ርግጫ
በመርፌ ቀዳዳ፣ ብትሾልክ ከድፍጥጫ
ዋ ሽተህ፣
ዋ ብትል፣
የሽንት ጎርፍ ነው፣ የጥምህ መቁረጫ።

ይህን ሁሉ ችለህ፣
በጥቂት ኮትኳቾች፣ ጠንተህ ብትፀድቅ
በፀሐይ እስትንፋስ፣ ብትወዛ ብትደምቅ
አንሰራራሁ እንዳልክ፣ አየሁ አዲስ ዓለም
ቅጠሎችህ ረግፈው፣ ቅርንጫፍህ የለም።

አይችሉትን ችለህ፣
ዳግመኛ ሥር ሰደህ፣
መክሰም መጠውለግን፣ ቀንጣት ሳትፈራ
ግንድህ አቆጥቁጦ፣ ፍሬ ስታፈራ
እልፍ ነው ቀጣፊህ፣ በሰልፍ በተራ።

ከቅጥፈቱ ናዳ፣ አፅምህን አትርፈህ
ከራስ በስትያ ስሌት፣ ዋርካነት አልመህ
ባሸለበች ፀሐይ፣ በነቃች ጨረቃ
ከትንሣኤህ ምኞት፣ ድንገት ስትነቃ
መንጋው ተሰልፏል፣ መጋዙን አሹሎ
ገዝግዞ ሊጥልህ፣ ከሥርህ መንግሎ።

ማክሰኞ 4 ኤፕሪል 2017

ተቀምጨ አያለሁ

አያለሁ ቁጭ ብዬ፣
ያለምን የጣር ምጥ
መድልዎና ሀፍረት
ወገኔ ጠውልጎ፣
ደምንባ ሲተፋ
አምኖ በከወነው፣
መልሶ ሲገፋ።

እመለከታለሁ፣
የህይወትን አተላ
እናት በልጆቿ፣ ተንቋሻ ተጥላ
ከመገፋት ብዛት፣
ሂዳ ስትጠለል ሞትን እንደጥላ።

እመለከታለሁ፣
ባፉ እንስት አጥማጅ፣ ከዳተኛ አማላይ
ጥሎሽ ነው እያለ፣
ግማሽ ጎኑን ሲያለብስ፣ ኦሜጋልባ ሰቃይ።

አያለሁ ጦርነት
ቸነፈር አያለሁ
አያለሁ አፈና
ስማእታት አያለሁ
አያለሁ እስረኞች
የግፍ ማራገፊያ፣
ዘብ አልባ ወደቦች።

ሕይን ሁሉ ስቃይ፣ እያየሁ ቆጥራለሁ
ጆሮዬን አቁሜ፣ ከልብ አደምጣለሁ
ቃል ካፌ ሳይወጣ፣ ጭጭ እንዳልኩ ሄዳለሁ።
እውን እኔ አለሁ?
________________________
መነሻ፣”I Sit and Look Out” —Walt Whitman

እኔን ብፈልገው

እንደ እፉዬ ገላ ፣ ቢቀለኝ ገላዬ
እንደ ህዋ ኮከብ ፣ ቢርቀኝ ጥላዬ
እንደ ሙታን መንደር ፣ ጭር ቢል ጓዳዬ
መንፈሴን አስሼ
ምናቤን ዳስሼ
ትግስቴ ተሟጦ ፣ መቅኔዬ ፈሷ'ልቆ
አየሁት ተንጋሎ ፣ እኔ ከእኔ ርቆ
ከዘመን ገደል ዉስጥ ፣ ተከስክሶ ወድቆ ።

እንደበራህ ለከሰምከው

ድቅድቁን ጥቁር ጨለማ ሰንጥቃ
ዛሬም ብርሃኗን ትለግሣለች ጨረቃ...

የማለዳ ኮከብም፣
እንደሁሌው ደማቅ ብሩህ ናት
ቀድማ ስትታይ ከንጋት ...

ፀሐይም እንደወትሮዋ ማልዳ ብቅ ትላለች
ፅጌረዳም ከደጃፌ ዛሬም ፀድቃ ትፈካለች...

ሰማዩ ዛሬም ሰማያዊ ነው
ወፎችም ይዘምራሉ
በቀስተደመና ክንፎች ላይ
ቢራቢሮዎችም ይደንሳሉ ...

ሁሉ ነገር እንደቀድሞው
አሁንም አለ ተንሰራፍቶ፥
ወዳጄ አንተ ብቻ የለህም፥
ከዚች ምድር ዳብዛህ ጠፍቶ።

ስለዚህ እኔን ከፍቶኛል፥
በምድራለሜ ደስታ ዘብቶ፥
ፈገግታም ከራቀኝ ሰንብቶ፥
ባንተ ሞት ውስጤ አንብቶ።
_________
መነሻ፣"To a Dead Friend", Langston Hughes
መታሰቢያነቱ፣ ላገኘው ስናፍቅ ሞቱን ለተረዳሁት ለዶ/ር ብርሃኑ ለገሠ።