በእኔና አንተ ምድር፣
ሆነህ አትፈጠር፣ ችግኝ ባለ ተስፋ
ከቶ ብቅ አትበል፣ በኮትኳች ልትፋፋ።
ባርባ ቀን እድልህ፣ ብታመልጥ ከ'ርግጫ
በመርፌ ቀዳዳ፣ ብትሾልክ ከድፍጥጫ
ዋ ሽተህ፣
ዋ ብትል፣
የሽንት ጎርፍ ነው፣ የጥምህ መቁረጫ።
ይህን ሁሉ ችለህ፣
በጥቂት ኮትኳቾች፣ ጠንተህ ብትፀድቅ
በፀሐይ እስትንፋስ፣ ብትወዛ ብትደምቅ
አንሰራራሁ እንዳልክ፣ አየሁ አዲስ ዓለም
ቅጠሎችህ ረግፈው፣ ቅርንጫፍህ የለም።
አይችሉትን ችለህ፣
ዳግመኛ ሥር ሰደህ፣
መክሰም መጠውለግን፣ ቀንጣት ሳትፈራ
ግንድህ አቆጥቁጦ፣ ፍሬ ስታፈራ
እልፍ ነው ቀጣፊህ፣ በሰልፍ በተራ።
ከቅጥፈቱ ናዳ፣ አፅምህን አትርፈህ
ከራስ በስትያ ስሌት፣ ዋርካነት አልመህ
ባሸለበች ፀሐይ፣ በነቃች ጨረቃ
ከትንሣኤህ ምኞት፣ ድንገት ስትነቃ
መንጋው ተሰልፏል፣ መጋዙን አሹሎ
ገዝግዞ ሊጥልህ፣ ከሥርህ መንግሎ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ