ሰኞ 14 ጁላይ 2014

በዚህ በጉድ አገር

በዚህ በጉድ አገር፣
መንገድ ላይ ማላመጥ ፣ ነውር በሆነበት
አደባባይ ቆሞ፣
እችግኝ ላይ መሽናት ፣ ማን ከልካይ አለበት።

በዚህ በጉድ አገር፣
በያደባባዩ፣
ባይነ-ህሊና ድሪያ ፣ ደም-ሥር ሲውጠረጠር
ስለወሲብ ማውጋት፣
በሹል ቃል አሳዶ ፣ ያስወጋል በነገር።

በዚህ በጉድ አገር፣
አንጀት ከድቶት ዝሎ ፣ ያገር ልጅ ሲያቃስት
ባርምሞ ምልከታ፣
ከንፈር መምጠጥ እንጂ ፣ ማን ከመጤፍ ቆጥሮት።

በዚህ በጉድ አገር፣
ጉልበተኛ ሲነጥቅ ፣ ላብ-አደር አፍኖ
መንገደኛው ያልፋል፣
በምን-ገዶኝ ግርዶሽ ፣ ማያዉን ሸፍኖ።

በዚህ በጉድ አገር፣
ጥራዝ-ነጠቅ ስያኝክ ፣ የቅልለትን ቅጠል
ትውልድ አሰልፎ፣
ያጠምቃል ሊህቁ ፣ የፍርሃትን ጠበል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ