ረቡዕ 26 ኖቬምበር 2014

ተመኘሁ

ታልቀረ መመኘት
ተመኘሁ ዛፍነት
ከላዬ አራግፌ ፣ ጥውልግ ቅጠሎቼን
ቅርንጫፎቼ አድገው ፣ አጠንክሬው ግንዴን
እንዳዲስ ፀድቄ ፣ ለምልሜ ዳግመኛ
ለቅዥቴ ሳይሆን ፣ ለህልሜ እንድተኛ።

ቅዳሜ 22 ኖቬምበር 2014

አውቃለሁ

እርግጥ ነው በድዬሻለሁ
እውነት ነው ጎድቼሻለሁ
ሁሉንም ጠንቅቄ አውቃለሁ።

በናፍቆት ሰቀቀን
በመገፋት ቆፈን
እንደማለዳ ዉርጭ እንሰፍስፌሻለሁ።
አውቃለሁ።

ዱካዬን አጥፍቼ በፈለግሽኝ ጊዜ
ሰው አልባ አድርጌሽ በወንዝሽ በወንዜ
እንደቆላ ሃሩር አጠውልጌሻለሁ።
ይህንንም አውቃለሁ።

ሆኘ ያልሁንሁትን
ኖሮኝ የሌለኝን
በቁሜ ስቃዥ በቀን
ክፉ ህልምሽ ሆኘ እንቅልፍሽን ነጥቄሻለሁ።
ይህንንም አውቃለሁ።

ዳብሼ ሌላ ገላ
ጎርሼ ሌላ ከንፈር
በቅናት ማዕበል አናውጬ አዳፍቼሻለሁ
ከሰው ተራ አሽቀንጥሬ ወርዉሬሻለሁ
ከመሃል ጎተቼ ወደ ዳር ገፍቼሻለሁ
ከንፈርሽን በጥርሶችሽ አስነከሼሻለሁ።
ይህንንም አውቃለሁ።

እቶን ወላፈኑ ከሩቅ በሚንቦገቦገው
በበደል ምጣድ ላይ አገላብጨሻለሁ
አሻሮ እስኪወጣሽ እስክታሪ አምሼሻለሁ
ይህንንም አውቃለሁ።

እርግጥ ነው በድዬሻለሁ
እውነት ነው ጎድቼሻለሁ
ሁሉንም ጠንቅቄ አውቃለሁ።

ዉስጥሽ ግን እንዲህ ሲል ሰማለሁ...

ከበደል ከስቃይ ከበቀል ባሻገር
እጅ ባፍ 'ሚያስጭን የረቀቀ ምሥጢር
በልብ የሚዳሰስ ከስሜት ጥላ ስር
ምህረት አይገደዉም እውነተኛ ፍቅር።

ሰኞ 17 ኖቬምበር 2014

ያልታደሉት አጤ

እጅ አልሰጥም ብለው ትኩስ እሳት የጨለጡ
አጤው ጉድ አላዩ በልጆቻቸው እንደተበለጡ 
እጅ ከእግር ሰጥተው በራድ ዉሃ እንደሚጠጡ።

ረቡዕ 12 ኖቬምበር 2014

ባመድ አፋሹ እጅሽ

ያኔ፣
የጎረሱትን አላምጠው ፣ አጣጥመው ሳይዉጡ
ያጎረሳቸዉን እጅሽን ፣ መልሰው ሊንከሱ ሲሮጡ
ፊትሽ በምሬት ከስሎ ፣ ገር እንጀትሽ እያረረ
ሀቀኛው እንደበትሽ ፣ ተከፍቶ እያማረረ
"እጄ አመድ አፋሽ ነው" ብለሽ ነግረሽን ነበረ።

ዛሬ፣
ባንቺው ቅጥ-አጥ ቅጥፈት ፣ ጅስሚያችንን ካበገንሽው
የመንደዳችንን ነበልባል ፣ ለቆፈንሽ ማክሰሚያ ከሞቅሽው
አደራ ንፋስ ሳይቀድምሽ ፣ አመዳችንንም እፈሽው

ሐሙስ 6 ኖቬምበር 2014

ተከልሎ ላይከለል

በሕመማችን ልክ ፣ ደዌዉን ለሚያፀዳ
በጥማታችን መጠን ፣ ወይን ጠጁን ለሚቀዳ
በጠኔያችን ስፍር ፣ ለሚቆርጥ ፍሪዳ
ላዛኝ ቅቤ አንጉዋቹ ፣ ለባዕድ እንግዳ
ገመና ሊከለል ፣ መንገዱ ቢፀዳ
ዛፉ ሳር ቅጠሉ ፣ ቢመስል ፀአዳ  
ያ'ፍታ እድፍ እንጂ ፣ ችግር ላይፀዳ
...
ፍስሃን ደስኩሮ ፣ እንደሄደ እንግዳው
በተማፅኖ ትእይንት ፣ ይደምቃል ጎዳናው
ባ'ዳፋ ደግ እጆች
ባ'ሳዛኝ ዉብ አይኖች
በ'ውነተኛዎቹ ፣ የህላዌ መልኮች
በመሰንበት ትግል ፣ ሕያ ምስክሮች።

ሰኞ 3 ኖቬምበር 2014

ዘመኑን ለገደለ

በስንፍና ጠብ-መንጃው ፣ አቀባብሎ እያለመ
ምትክ-አልባ ዘመኑን ፣ አከታትሎ ላጋደመ
ጅብዱዉን ቆሞ ቢተርክ ፣ <<ካለ'ኔ ጀግና>> እያለ
ቁልቁል በሚያየው ግዳይ ዉስጥ ፣ እልፍ የራሱ ሞት አለ።