ከላይ የጠል ቁጣ
ከታች ምድር ቀልጣ
ላቤን ከጅማቴ ጠልቄ ቀዳለሁ
ከ'ሷ ጀርባ ቆሜ ተራ ጠብቃለሁ...
አርሳው ወይ ሸምታው ያልለየለት ጠጉሯ፣
መቃ አንገቷን ታ'ኮ
ችቦ'ገቧን አንቆ
ጉብታዉን ተንተርሶ
ሸለቆውን ባይኑ ልሶ
አደናቀፋት ስል ፣ አጋደማት ጠልፎ
ሽቅብ ይታዘባል ፣ ከቋንጃዋ አርፎ...
ሹክ ያልኳት ይመስል፣
ወደ ጎምዢው ፊቴ ፣ ፊቷን ብታዞረው
ቅፅበታዊ ቆፈን ፣ ጅስሚየን ወረረው...
ጉድ እኮ ነው!
ያጠመቀኝ ላቤ ወደ ላይ ተነነ?
የጠሃይዋ ቁጣ ከምኔው መነነ?
አሁን በዚህ ፍጥነት ፣ ተፈጥሮ ተዛባ?
ወይስ እዚሁ ቆሜ ፣ ክረምት ዘሎ ገባ?
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ