ረቡዕ 15 ማርች 2017

አንድ ሰው

በህልምሽ ከፍቶሽ ስታነቢ፣
በ'ዉኑ እምባሽን 'ሚያብስ
ሌሎች ጊዜሽን ሲሻሙ፣
እርሱ እድሜውን 'ሚሰጥሽ
በአደይ ዝንታለም መስክ፣
የደስታሽን ዘር 'ሚዘራ
ነፍሱ የማትለመልም፣
አዝመራሽ ፍሬ ሳያፈራ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።


ካፅናፍ አፅናፍ ቢንቆረቆር፣
የለቅሶሽ ርዝመት 'ማይገደው
ይልቅ እንባሽን ሰብስቦ፣
በሙቅ ተንፋሹ 'ሚያደርቀው
በዘመን ማማ ላይ ሆኖ፣
ዘመንሽን በልቡ 'ሚነካ
ፅልመትሽን ወዲያ ፈንግሎ፣
ደመና ምናብሽን 'ሚያፈካ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።

ከስኬትሽ ፌሽታ ማልዶ፣
ዘልቆ ሕልምሽን ያለመ
ከመከናወንሽ ቀድሞ ሄዶ፣
ዛሬ-ነገሽን የተለመ
በንፍገት የታፈገ አየር፣
በተስፋ ሉባንጃ 'ሚቀይር
ከከፈለው ዋጋ ቀድሞ፣
የፍቅርሽን በረከት 'ሚቆጥር...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።

እጆችሽ በቆፈን ቆርብተው፣
የሙቀት ጠኔ ሲያበግናቸው
እጆቹ መድሃኒት ሆነው፣
ህዋሶችሽን 'ሚያክማቸው
የድዌ ፉፉቴ ሲገርፍሽ፣
ፈውስና ሠላም 'ሚጣራ
የዶፉን ድቅድቅ ሰንጥቆ፣
ፈገግታን ከፊትሽ 'ሚያበራ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።

መነሻ: "Invisible Kisses" by Lemn Sissay

ሐሙስ 9 ማርች 2017

ከወርቅነት ወዲያ

አእላፍ ነው ዝምታ፣
በገለባ ቃላት
ባንገት በላይ ቅርሻት
በሃሜት ሹል ምላስ፣ በባዶ ድንፋታ
ግርማዊ ጥልቀቱ፣ ከቶ 'ማይረታ።

*****

ዝምታ ዉበት ነው፣
የእውነት ስብሃቷ
የሀቅ ደም ግባቷ
ያለም ጆሮ ቢቆም፣
ኡኡ አለማለቷ።

*****

ሰላም ነው ዝምታ፣
ፍፁም ብፁዕ እረፍት
ሀሴት ነው ዝምታ፣
የምናበ-ሹለት መመዘኛ ልኬት
የሕይወት ቅራሪ ከቶ ያልበረዘው
የንዋይ ሆምጣጤ ወትሮ ያልመረዘው።

*****

እንባ ዝም ያለ ነው፣
የአዞ ካልሆነ
ፈገግታም ዘም ያለ፣
ካንጀት ከበቀለ
ፍቅር ዝም ያለ ነው፣
ሲሆን ምክንያት አልባ
ሞትም መጥቶ ሲወስድ፣
በዝምታ ጩሀት፣ቀጥሮ ሳያግባባ።

ረቡዕ 8 ማርች 2017

ፍረጃ ህላዌ

ተናፍቆ ተናፍቆ፣
ሌት በቀን ሲተካ
ሞት መጥቶ ሲሰየም፣
በሕይወት መሥመር ዱካ
ሟች ሟችን አክሞ፣
ሟች ሟችን ሲያድነው
ሟች ሟችን አስታሞ፣
ሟች ሟችን ሲቀብረው
በትዉልድ ሰንሰለት፣ሰው በሰው ሲቀጠል
ለችግኝ መለምለም፣ጋሻ ዛፍ ሲቃጠል
በትርትሯ መሳ ጠብቃ መሰፋቷ
ላልጨበጥነው አልፋ ኦሜጋ አልባነቷ።