በህልምሽ ከፍቶሽ ስታነቢ፣
በ'ዉኑ እምባሽን 'ሚያብስ
ሌሎች ጊዜሽን ሲሻሙ፣
እርሱ እድሜውን 'ሚሰጥሽ
በአደይ ዝንታለም መስክ፣
የደስታሽን ዘር 'ሚዘራ
ነፍሱ የማትለመልም፣
አዝመራሽ ፍሬ ሳያፈራ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።
ካፅናፍ አፅናፍ ቢንቆረቆር፣
የለቅሶሽ ርዝመት 'ማይገደው
ይልቅ እንባሽን ሰብስቦ፣
በሙቅ ተንፋሹ 'ሚያደርቀው
በዘመን ማማ ላይ ሆኖ፣
ዘመንሽን በልቡ 'ሚነካ
ፅልመትሽን ወዲያ ፈንግሎ፣
ደመና ምናብሽን 'ሚያፈካ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።
ከስኬትሽ ፌሽታ ማልዶ፣
ዘልቆ ሕልምሽን ያለመ
ከመከናወንሽ ቀድሞ ሄዶ፣
ዛሬ-ነገሽን የተለመ
በንፍገት የታፈገ አየር፣
በተስፋ ሉባንጃ 'ሚቀይር
ከከፈለው ዋጋ ቀድሞ፣
የፍቅርሽን በረከት 'ሚቆጥር...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።
እጆችሽ በቆፈን ቆርብተው፣
የሙቀት ጠኔ ሲያበግናቸው
እጆቹ መድሃኒት ሆነው፣
ህዋሶችሽን 'ሚያክማቸው
የድዌ ፉፉቴ ሲገርፍሽ፣
ፈውስና ሠላም 'ሚጣራ
የዶፉን ድቅድቅ ሰንጥቆ፣
ፈገግታን ከፊትሽ 'ሚያበራ...
ፍቅሩ ቁንጥር ያይደለ
ከእልፍ አእላፍ የዘለለ
እመኚኝ አንድ ሰው አለ።
መነሻ: "Invisible Kisses" by Lemn Sissay
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ