ሐሙስ 9 ማርች 2017

ከወርቅነት ወዲያ

አእላፍ ነው ዝምታ፣
በገለባ ቃላት
ባንገት በላይ ቅርሻት
በሃሜት ሹል ምላስ፣ በባዶ ድንፋታ
ግርማዊ ጥልቀቱ፣ ከቶ 'ማይረታ።

*****

ዝምታ ዉበት ነው፣
የእውነት ስብሃቷ
የሀቅ ደም ግባቷ
ያለም ጆሮ ቢቆም፣
ኡኡ አለማለቷ።

*****

ሰላም ነው ዝምታ፣
ፍፁም ብፁዕ እረፍት
ሀሴት ነው ዝምታ፣
የምናበ-ሹለት መመዘኛ ልኬት
የሕይወት ቅራሪ ከቶ ያልበረዘው
የንዋይ ሆምጣጤ ወትሮ ያልመረዘው።

*****

እንባ ዝም ያለ ነው፣
የአዞ ካልሆነ
ፈገግታም ዘም ያለ፣
ካንጀት ከበቀለ
ፍቅር ዝም ያለ ነው፣
ሲሆን ምክንያት አልባ
ሞትም መጥቶ ሲወስድ፣
በዝምታ ጩሀት፣ቀጥሮ ሳያግባባ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ