ዓርብ 15 ጁላይ 2016

ርእደ-ሃሳብ

ጉዞዋን እንደምትጠነስስ፣ የማዕበል ጌሾ ቀንጥሳ
የፍዳ ባህር እንደምትገምስ፣ እንዳ'ንዲት ባለህልም ዓሣ ...

ልብን በሀሴት ሰንጥቃ
እስትንፋስ ከሥጋ ነጥቃ
ከእንቁ ልሳን ተወርውራ፣ ከክምር ጫጫታ መሃል
ነፍስን እንደምታክም፣ አንዳ'ንዲት ደመ-ሙሉ ቃል ...

ሲሻት የዘመን ፅልመት፣ በቅፅበት 'ምትደመስስ
ሲላት ያለምን እሳት፣ በ"እፍ"ታ 'ምትለኩስ
በጣቶች እቅፍ እንዳለች፣ እንዳ'ንዲት የክብሪት እንጨት ...

ላቅመ-መነገር ያልበቁ
ካልኳቸው ሺ'ጥፍ የላቁ
የህሊናዬን ግድግዳ፣ሳይታክቱ 'ሚደልቁ
እኒያ የብረት ኳሶች
እኒያ የሃሳብ ቦክሶች
ዉስጤን ፈንቅለው ቢወጡ
ምድርን ባንቀጠቀጡ
ፀሐይን ባቀለጡ።

ቅዳሜ 2 ጁላይ 2016

ግዴለም ይቅርብን

ግዴለም ይቅርብን ...
የመውደድ አዝመራ ማጨድ አልቻልንና
የቅጥፈት ቄጤማ መንቀል ተካንንና...
ግዴለም ይቅርብን...
ክህደት እምነት ይሁን
ጥላቻው ንፁህ ፍቅር
ሰማዩ ዝግ ጣሪያ
ሜዳው የግንብ አጥር።

ዓርብ 3 ጁን 2016

ጠርጥር

አንተና አንተ ብቻ፣ ተፋጣችሁ ሳለ
አንተ ስትጠራው፣ አንተ 'አቤት' ካለ
ግዴለህም ጠርጥር፣
ገደል የሆንህለት፣ ማሚቶህ እንዳለ።

ዓርብ 22 ኤፕሪል 2016

አይገርምሽም?

ድልድዩ ዋዣቂ፣
ካለት ሲያነክተን
ወንዙም ችኩል ደራሽ፣
ከግንድ ሲያላትመን
ባሕሩም ሞገደኛ፣
መርከብ ሲያስታቅፈን...
ህዋስሽ ህዋሴ፣
ነፍስሽና ነፍሴ፣
በዉዥንብር ናዳ፣ ሲልሙ ሲደቅቁ
አይገርምሽም ዉዴ፣
ቃልሽ ከቃሌ ጋር፣ እንዲህ መጣበቁ።

ምሽት ነበር

የኦሪዮን ክዋክብቱ፣
ርጌልና ቤቴልጌስ፣
ነጥተው ገዝፈው የቀሉበት
ምሽት ነበር፣ዉድ ምሽት
ዋጋው ካልማዝ ከ'ንቁ በላይ
ከፊቴና ከፊትሽ ላይ
ወዙ ደምቆ ፈክቶ ሚታይ።
ምሽት ነበር አይረሴ፣ ተስፋው ከማር የጣፈጠ
ለመግባባት ስንታገል፣ ሳንጨብጠው ያመለጠ።

አብረን ነበርን

ድልድይ ሆኖልሽ አልፈሽ፣ የኔ ሰፊ ትከሻ 
ያን የሰማይ ጉማጅ፣ ጣልሽው ባንዲት ጥቅሻ
እኔስ ምኔ ሞኝ ነው፣ ብድር ባየር መላሹ
በምድር አፈር ሳልቦካ፣ ነገን ዛሬ ቀያሹ 
እረፍት አልባ አይኖቼን፣ በትከሻሽ አሻግሬ 
ምርኮ አሰልፌ መጣሁ፣ ሳያገሳ ምንሽሬ።

ቅዳሜ 27 ፌብሩዋሪ 2016

ምነው?

የክቡር ሰውነት እፍታው
የሁሉ እኩልነት ወለላው
ያብሮነት የፍቅር አምሳሉ
የመተባበር ቤተ ቀንዲሉ
ሲረግፍ አካሉ እንደቅጠል
ሲደርሰው እሳት እንደጠበል
ወትሮ እንተባበር ባይ ሁላ
ምነው እሸት ቃሉን ቀጥፎ በላ?
ምነው ጋን አንደበቱ ተዘጋ?
ምነው ዝምታን አወጋ?
የምር ይህ ወገን የኛ ነው?
ከምር አንድነት የእውነት ነው?
ዲስኩር ተምግባር መገናኛው
ያብሮነት ሀገሩስ ወዴት ነው?

ቅዳሜ 30 ጃንዋሪ 2016

የተቃርኖ ማማ

በሰጠምኩኝ መጠን ስንሳፈፍ
ከመናፍቅነት ገለባ ተበጥሬ ሳልፍ
ገላየ በልብ ከልብ ቀልጦ
ልቤ ከነፍስ ባህር ሰምጦ
ነፍሴ በፍቅር ቅመም ተላቁጦ
ገላዬ ማሳ ሆኖለት
ህመሜ ተዘራ ታጨደ
መድሃኒት ብዬ የዋጥኩት
ማዳበሪያ ሆኖለት ቀለደ።

ዋጋ

ሰርቆ ሳሚ ሲመጣ፣ ተይው በብላሽ ይላስሽ
የኔ ተራ ሲሆን ግን፣ ዋጋው ይናር ከንፈርሽ
ወሮ በላን ስትከሽው፣ ይቅር በይው ለምነትሽ
የኔ ወንጀል ሲሆን ግን፣ አይቀጡ ቅጣት ይኑርሽ።

አታሚ

ብቻዬን ከብቸኘት ስታገል
ፍርሃቴ ፍም አውጥቶ ሲንበለበል
ያ የስንብት አዋጅሽ
ያ የ "ደህና ሁን" ፍርድሽ
ልክ እንዳላዩት ሩቅ ሀገር
እንዳልገለጡት መፅሐፍ
እንዳልጠገኑት ሰባራ ልብ
እንዳላበሱት የንባ ዘለላ
ሰርክ የናፍቆት ጌሾ ነው፣
ዘሎ ፊጥ 'ሚል ከራሴ
ዞትር የቁጭት ጅራፍ ነው፣
ሰንበር አታሚ ከመንፈሴ።

ክፋቱ

ጨለማው ፍፁም ሳይፀልም
ብርሃኑም እጅግ ሳይለመልም
በተስፋ ነበልባል በእምነት
በጥርጣሬ ሰይፍ በፍርሃት
ስለመንደዱ ስለመድማቱ
ልብ ልብ አለማለቱ
ዘግይቶ ማወቅ ክፋቱ።

ኩ!

ቱግ ብዬ ተንተክትኬ
ከቆምኩበት ተፈትልኬ
ወረድኩኝ ከወንዛ ወንዙ
ሰከንኩኝ ካፍ ከገደፉ
ብለኩሰው አይበራ
ብደግፈው አይጠና
ብቆሰቁሰው ተዳፍኖ
ብኮተኩተው መንምኖ
ያሳብ ጠኔ ደልቆኝ
ያንጎል አፅሜን አድቅቆኝ
በደራሽ ድፍረት ተሞልቼ
ያሳብ ብስናዬን አግስቼ
ተወርውሬ ከዉሃው እንዳረፍኩ
እግዚኦ ከምኔው ሰጠምኩ
አበስኩ!
ገበርኩ!