ሰኞ 30 ኦክቶበር 2017

አርዶ አደሮች ሆይ

ባሩድ እንደጠበል፣ በጅምላ እየረጩ
አረም ለማቆየት፣ ቡቃያ እየቀጩ
በደም ቀይ ምንጣፍ፣ ዛሬን ቢራመዱ
ነገ ሸንጎ 'ሚቀርብ፣ ዶሴ ነው መንገዱ።

ቢሆንም ባይሆንም

የህልማለም ድግስ፣
ህላዌን አንጥሮ፣ ቢያጠጣም ቅቤ
አዋዝቶ ቢያጎርስም፣ ክትፎን ከአይቤ
ሰው ምኑ ሞኝ ነው፣
ገር ሕልሙን ተማምኖ፣ አይተኛ በራብ-ጥም
ጉምዥት ሳይጎነጭ፣ ተስፋ ሳይቆረጥም።

እኔን ሲዳኝ እኔ

አህያን ከጅብ ሳጣጥም
አይጥን ከድመት ሳሳስም
ዲስኩሬ በዉድ ሲያዋድድ
ፍም እሳትን ከደረቅ ጭድ
ልሣኔ ፈልጎ አቃርቦ
አራምባዉን ከቆቦ
ግና ምን አገኘኝ፣ ጎደልኩት ከራሴ
ደርሶ የሚከዳኝ፣ ጥሬ ቆይ ምላሴ።

ዉሃ ወቀጣ

ልቦና ታውሮ፣ አይን ሲያክል ጨረቃ
ሳሙና ፈልሳፊው፣ ሲሆን ታጥቦ ጭቃ
ማሰብ ምን ሊረባ፣ መፅዳትስ ለምኔ
ተጨምቆ ላይወጣ፣ ፅድቅ ከኩነኔ።

ረቡዕ 25 ኦክቶበር 2017

በጫጉላ ጨረቃ

የናፍቆትን ጋራ፣ አሟምተሽ ስታልፊ
የትዝታን ግርዶሽ፣ ገላልጠሽ ስትገፊ
ድካምሽን ለማከም፣ በቀኝሽ ስታርፊ
የእንቅልፍ መንኩራኩር፣ ይዞሽ ሲመነጠቅ
የህልም ሰረገላ፣ አሳፍሮሽ ሲነጠቅ
ከማረፊያሽ ልቤ፣ ሰገነት ቁጭ እንዳልሽ
ያ'እዋፍ ሕብረ-ዜማ፣ ቀስቅሶ ካነቃሽ
ይልቅ ጆሮ ስጪ፣ ለማለዳው ዜማ
አዋጅ ይዟልና፣
በኔ የሚነገር፣ ባንቺ የሚሰማ።

ልፋ ያለው ምናብ

ልቦና ታውሮ፣ አይን ሲያክል ጨረቃ
ሳሙና ፈልሳፊው፣ ሲሆን ታጥቦ ጭቃ
ማሰብ ምን ሊረባ፣ መፅዳትስ ለምኔ
ተጨምቆ ላይወጣ፣ ፅድቅ ከኩነኔ።