ማክሰኞ 26 ዲሴምበር 2017

ለብርቱ ትከሾች እጅ መንሻ

"ወጡ ቀለም ሆኖ እንጀራው ብራና
ይድረሰኝ ደብዳቤ ተርቢያለሁና"
ብሉ እንዳልማለደ
ንፋስን አማላጅ፣
ጨረቃን አዋላጅ፣
አርጎ እንዳልነጎደ
ገብሬ ኢልማ ደስታ እንደዘበት ሄደ
ኦክላሆማ ሜዳን ቤት አርጎት ለመደ።

ከዴህሊ እስከ ሎንዶን
ከይፋት እስከ ዋሽንግቶን
ባሻ አሸብር ባለ ቧልቱ
ደማሙ ብእረኛ አብዬ መንግስቱ
ያለ ፕሮብሌም አርፎ መተኛቱ!

ዮሐንስም ሄደ፣ ሰፊ አድማሱን አስታቅፎን
"እስኪ እናንተ ጎዱች ተጠየቁ" ብሎን
በብቸኝነት ነበልባል እንደነደደ
ቅኔው ይፋቴ ዳኛቸዉም ነጎደ
ኡኡታ አሮበት "እምቧ በሉ" እያለ
የጉራማይሌ ሕልሙን፣ ቁጭት እየፈተለ
ዮናስ በኩርምት ሞቱ እያሳለው ተከተለ
"እግዚያአብሔር ትመስን፣ ክብሯ ይስፋ" እንዳለ።

ደበበ በምናቡ ስይፍ ክትፎኛ ተካትፎ
ገሞራው በረከትን ሼጣንኛ ተራግሞ
የዜሮን ቁጥርነት ከአልፋው ሞግቶ
እውነት ለሚያንቀው አገጭ ይዞ ግቶ
ከዑራኤል ዳገት ሽቅብ እየቃኘን
"እኔም እንደናንተ ሕያው ነበርኩ" አለን።

አያ ሙሌም ምህላዉን ታክቶ
አጅሬው ከመንበሩ መኖሩን ሞግቶ
ክልትው አለ ብቻዉን፣ አዘመራውን እንደነዛ
በሱ የደም ጠብታ፣ የስንቱን ግንባር ሊያወዛ።

ከአባ ገዳ ኢልማ ገልማ
የማይድን በሽታ ነፍሱ አስታማ
ከመርካቶ እስከ ኮምፔሽታቶ
ከመቅደላ እስከ ላሊበላ
ከኢዞፕ እስከ ኢቶፕ
ከሐምሌት እስከ ኦቴሎ
ያ ፀጋዬ ማሎ ማሎ።

ከጩታ እስከ ፓሪስ
ከዊንጌት እስከ ምኒያፖሊስ
ልጅነቱን አነባብሮ
ዘበት እልፊቱን ተሻግሮ
ለብስለት ወዜማ ተቃጥሮ
ወለልቱው ስሎሞን ላይመተር ረዘመ
በዉርጭማ ሰማይ ላይጨበጥ ተመመ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ