የዛሬ ስንት ዓመት ፣ በነፃነት ማግስት
ህሊና ገጠመ ፣ ከሆዱ ጋር ሙግት
ከየጎራው ወጡ ፣ የፍትህ አማልክት።
ያልታወረ ህሊና ፣ ብሩህ ያገር ተስፋ
ሊቀጥል አላሻም ፣ወትሮ እንደተከፋ።
የሰላምን እሳት ፣ ላንቃዎች ለኮሱ
ብዕሮችም አልቀሩ ፣ እንደመነኮሱ።
የማይዝሉ አጆች ፣ የማይደክም አንደበት
ማን ሊመልሳቸው ፣ አብረው ባንድነት።
ህሊና ተርቦ ፣ ሆድ ከሚቀፈደድ
ባድር ባዮች ሴራ ፣ ሁሌ ከመሳደድ
ሳይሻል አይቀርም ፣ ጨርቅ ጥሎ ማበድ።
እብድስ ከለየለት ፣ ማንም ያዝንለታል
ጨርቁን እንኳን ቢጥል ፣ ዉራጅ ያለብሱታል
የሚበላው ቢያጣ ፣ ሰይጣን ያጎርሰዋል
አዉቆ አበድ መሆን ነው ፣ ከሁሉ 'ሚያስጠላ
እርባና የሌለው ፣ የሰው ቀጥፎ-በላ።
እብዶችም አይደሉ ፣ ወይ አውቆ አበዶች
ወገንም አይደሉ ፣ ወይ ጠላት መሳዮች
ከዚህ እየወሰዱ ፣ ከዚያ አቀባዮች
ከዚህ እየነቀሉ ፣ ከወዲያ ተካዮች
ከዚህ እያቦኩ ፣ ከዚያ ጋጋሪዎች
እዉነት ትፍረዳቸው ፣ እኚህን ጡት ነካሾች ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ