ሕይወት ማለት ፣
ሕይወት እኮ ሙዚቃ ናት ፣
በረቂቅ ቅኝት የምታዜማት
በዉብ ቅላፄ የምታስጌጣት ፣
ጉዳት ሲጨብጥህ ትተክዝባት ፣
ፍርሃት ሲከጅልህ ትፎክርባት ፣
ፌሽታ ሲነሽጥህ ትፈነጥዝባት።
አየህ ወዳጄ ፣
ሕይወት ማለት፣
ሕይወት እኮ ዉድድር ናት ፣
ህሊና በሚባል የራስ ዳኛ፣
በሕግጋት የምትመራ
መሸነፍ የሚሉት ፅልመት ፣
ማሸነፍ የሚባል ንጋት ፣
በፈረቃ የሚያደምቋት
ወጪ ወራጁን እምታሳይ ፣
የፍትጊያ አውድማ ናት።
እና ወዳጄ ፣
ሕይወት ማለት ፣
ሕይወት እኮ መስዋዕትነት ናት ፣
እንዳሻህ በብላሽ ፣ ከየትም የማታፍሳት
ወገብህን ሸብ ጠበቅ አርገህ ፣
ጥፍርህ አስኪቆስል ዳገት ቧጠህ ፣
ወደ ማምሻው ነው የምትቆናጠጣት።
ስማኝማ ወዳጄ ፣
ሕይወት ማለት ፣
ሕይወት እኮ ቅኔ ናት ፣
ያለ ጠብ-መንጃ ዘርፈህ ፣
በቀለጠው ሰሟ ተውልዉለህ ፣
በነጠረው ወርቋ ትደምቅባት።
ከምንም በላይ ወዳጄ ፣
ሕይወት ማለት ፣
ሕይወት እኮ ፍቅር ናት ፣
በቁሳቁስ ቅራቅንቦ ፣ በንዋይ የማትለካት ፣
ሳትሰጥ ተቀብለህ ፣ ሳትቀበል የምትሰጣት።
(የበድሉ ዋቅጅራን "ሀገር ማለት የኔ ልጅ" በማሰብ የተፃፈ)
good
ምላሽ ይስጡሰርዝtnxs!
ሰርዝይህ ልጥፍ በጸኃፊው አስተዳዳሪው ተወግዷል።
ምላሽ ይስጡሰርዝ