እሑድ 13 ኤፕሪል 2014

አንቺ'ኮ

አንቺ'ኮ እጡብ ድንቅ ነሽ፣
እውነት የእውነት ነሽ፣
ከልብሽ አይናማ'ኮ ነሽ።
ሙሉ ጉባኤ ሲስቅልኝ
ፈገግታዬን ሲያፀድክልኝ፣    
ሰርስረሽና ጎርጉረሽ
ልቅም አርገሽ አበጥረሽ
አንግዋለሽና አንጥረሽ ፣
ከሚያስንቅ ግዙፍ ጋራ    
ከክምር ፈገግታዬ ተራ
ያዘኔን እሾህ ትመዣለሽ።

አንቺ'ኮ እጡብ ድንቅ ነሽ፣
እውነት የእውነት ነሽ፣
ከልብሽ አይናማ'ኮ ነሽ።
ተሰፍቶ ጥርሴ ከከንፈር
ወይ አልናገር ወይ አልጋገር
"ጋግርታሙ!" ሲለኝ አገር፣
ሳልተነፍስ ሽራፊ ቃል
ጠጠር ከልሳኔ ሳልወረውር፣
ፀጥ ያለዉን ፀጥታዬን
ልቤ ላይ ጆሮሽን ደቅነሽ
የጥሞና አደማጬ ነሽ።

አንቺ'ኮ እጡብ ድንቅ ነሽ፣
እውነት የእውነት ነሽ፣
ከልብሽ አይናማ'ኮ ነሽ።
እሳት ለብሼ እሳት ጎርሼ
ሳስቸግር ለያዥ ለገራዥ፣
ደሜ ሞቆ ሲያተኩስ
ቀረርቶዬ ሞልቶ ሲፈስ፣  
ከንዴቴ ነበልባል ወስደሽ
የእሳት ደመና ሰርተሽ  
የፍቅር ዶፍ ታዘንቢያለሽ።

አንቺ'ኮ እጡብ ድንቅ ነሽ፣
እውነት የእውነት ነሽ፣
ከልብሽ አይናማ'ኮ ነሽ።
በስስት ሲቃ ሳቃስት
አይኔ ከማዶ ሲቃትት፣
ጨረቃን በምናቤ ሳቅፍ
ክዋክብት ከሰማይ ሳረግፍ፣
ስሜት ሲያረገኝ ወፈፍ
ከንፈሬ ከንፈርሽን አፈፍ፣
በሃሴት ቀልጬ ስከንፍ
በንዝረት ባህር ስንሳፈፍ፣      
ስትዳባብሽኝ ባይኖችሽ
የናፍቆትን ጉም በትነሽ
የርካታ ጠበል ትረጫለሽ።

አንቺ'ኮ እጡብ ድንቅ ነሽ፣
እውነት የእውነት ነሽ፣
ከልብሽ አይናማ'ኮ ነሽ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ