ያ ጓዴና እኔ፣ ፊትለፊት ተያየን
"ወዴት ነህ ? "ተባባልን
ኢላማ ግባችን እንድነቱን አወቅን።
ፅዋችንን ሞልተነው
ለድላችን ከፍ አርገነው
አጋጭተንም ቀመስነው።
የጉምዝዝ ጣፋጭ ነው
ባንዳፍታም ፉት አልነው
ለጥቀን ጨ...ለ...ጥ...ነ...ው።
አልኩኝ በሞቅታ ... "እ-ና-ሸ-ን-ፋ-ለ-ን!"
ቀጠለና ጓዴም ... "እ-ና-ቸ-ን-ፋ-ለ-ን!"
ስንሸልል ፣ ስንፎልል ፣ ሳይገድረን እንቅልፍ
አንዳች ድምፅ ሰማን እሳት 'ሚያርከፈክፍ።
የሰደድ እሳቱ ዘንቦ ... ዘንቦ ... ዘንቦ!
ቡቃያውን መርጦ በቀይ ጎርፍ አጥቦ
የረገፈው ረግፎ ፣ የተረፈው ተርፎ
የደለል ሙላቱ አንጉዋሎ አንሳፎ
እኔም ተ-ሸ-ን-ፌ ፣ ጓዴም ተ-ቸ-ን-ፎ
ያለያየን መንገድ ባንድ ላይ ጠቅሎን
በስደት ታንኳ ላይ ዳግም አገናኘን።
ያ ጓዴና እኔ ፣ ዛሬም አልተማርን
ያ የቃል እባጩ ፣ ሶንኮፉ አልወጣልን
በሽንፈታችን ዉስጥ ... "እ-ና-ሸ-ን-ፋ-ለ-ን!"
በችንፈታችን ዉስጥ ... "እ-ና-ቸ-ን-ፋ-ለ-ን!"
እያልን ዛሬም "አለን"።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ