"ቀለም የዘለቀኝ" - ብለህ ካልተኮፈስህ
ካፈር መደቡ ላይ - አብረህ ከተሰየምህ
የከተበልህን - እንቶኔ አሰማምሮ
የለቃቀምከውን - ዙረህ እንደ ጭራሮ
ወረቀት ከብእር - የግድ ሳያዋድድ
ከህሊናው ማህደር - ይቀዳዋል ለጉድ።
ትረካ በእጁ - ማዋዛት በደጁ
ምን ብዥታ ቢብስ - በንቅልፍ ቢያንጎላጁ
የኋሊት ለማየት - አይኖቹ አያረጁ።
"እኔ አውቅልህ" ብሎ - ባዕድ የጋተህን
"ወገኔ" ምትለው - ያወላገደውን
የታሪክ ጠቃሚው - የደራረተውን
ቀንና ሰዓቱ - ሳይዛነፍ ውሉ
ሳይለቅ ቀለሙ - ሳይደበዝዝ ምስሉ
በትዝታ ፈረስ - በዘመን ኮርቻ
አፈናጦ ሚያደርስ - ከኩነት ዳርቻ
ላገሬ ባላገር አጣሁለት አቻ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ